በኃጢያት ምክንያት እግዚአብሔር ተለይቶናል?
በፍፁም! እግዚአብሔር ከሰው ጋር ተለያይቶ አያውቅም። ከሰው ተደብቆ አያውቅም። መለያየት በሰዎች አዕምሮ ውስጥ የተፈጠረ የተሳሳተ አመለካከት ነው። የመለያየት ትምህርት ከምናልፍበት ጊዜያዊ ስሜት የተፈበረከ የውሸት እውቀት ነው።
አዳም ኃጢአትን ወደ አዕምሮ አስገብቶ ሲያምን (ፍሬውን ሲበላ) ከእግዚአብሔር ሸሸ እንጂ እግዚአብሔር ከአዳም አልሸሸም።(ዘፍ3:8) እግዚአብሔር መልካም ሰርተህልኛል ብሎ ያልቀረበውን ሰው ክፉ አድርገሀል ብሎ አይለየውም። አዳም ተደበቀ እንጂ እግዚአብሔር አልተደበቀም። አዳም ራቁቴን ነኝ አለ እንጂ እግዚአብሔር ራቁትህን ነህ አላለውም። (ዘፍ3:7)
እንዲያውም “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ?" የእግዚአብሔር ጥያቄ ነበር።(ዘፍ3:11) ራቁትነት በእግዚአብሔር የተረጋገጠ እውነት ሳይሆን በሰው የታመነ #የውሸት_እውቀት ነው። ራቁትነት ከእባቡ (ዲያቢሎስ) ስለ ማንነታችን የተነገረን የውሸት እውቀት ነው። ኃጢያት ማለት አምነን የተቀበልነው ራቁቴን ነኝ የሚል የውሸት እውቀት ነው።
ኃጢአት በሰው ውስጥ ኮነኔን ይፈጥራል። ነገር ግን እኛ ስለተኮነንን እግዚአብሔር አፍሮብናል ማለት አይደለም። እኛ ስለ ማንነታችን ውሸትን አምነናል ማለት እግዚአብሔርም ስለ እኛ ውሸት ያምናል ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ከአዳም ውድቀት በፊትም ሆነ በኃላ ስለ አዳም ያለው አመለካከት የፀና ነው። አዳም በመልኩና በአምሳሉ የወለደው ልጁ ነው። (ዘፍ1:27፣ሉቃ3:38)
ልጅ ጭቃ ነካ ተብሎ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ አይጨመርም። ወርቅ ስለ ቆሸሸ ክብሩን አያጣም። አብርሀም አጋር ቤት ስለ ገባ ታላቅ ዋጋው ዝቅ አይልም።(ዘፍ15:1) ከ100 በጎች መሀከል አንዱ ተለይቶ የጠፍ በግ እንጂ ወደ ተኩላነት አይቀየርም።(ሉቃ15:6) ንስር ከዶሮ ጋር ስላደገ ዶሮ አይሆንም። ልጅ ከአባቱ ንብረት ወስዶ በማጋጣነት ስላባከነ ባሪያ አይሆንም።(ሉቃ15:24) አዳምም ፍሬዋን ስለበላ የእግዚአብሔር መልክ አያጣም። #case_closed
ማንነታችን መፍትሔ የሚያስፈልገው ምንም አይነት ችግር የለበትም። የአዳም ፍሬውን መብላት ችግር የፈጠረው እግዚአብሔር ለአዳም ያለው አመላካከት ላይ ሳይሆን አዳም ስለ ራሱ ያለው አመለካከት ላይ ነው። የተፈጠረው ችግር ሁሉ የተፈጠረው የአዳም አመለካከት ውስጥ ነው። እግዚአብሔር አዳምን ቆዳ ያለበሰው እርሱ ስለ አዳም ያለውን አመለካከት ለመቀየር አይደለም። ነገር ግን አዳም ስለ ራሱ ያለውን የራቁትነት አመለካከት እንዲቀይር ነው።
አዳም እግዚአብሔር ፍሬውን ስለበላው ይጠላኛል ብሎ ያምናል። ውሸት! ሰዎች እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት ሰውን ይተዋል ብለን እናምናለን። ውሸት! የምንሸሸው እኛ ነን እግዚአብሔር ከሰው ተለይቶ አይውቅም። ይህም ዳዊት ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ብሎ እንደዘመረው ነው። (መዝ 139:7)
ኢየሱስ የመጣው የዲያቢሎስ ስራ ሊያፈርስ ነው።(1ዮሐ3:9) የእባቡን ራስ (የውሸት ትምህርት) ለመርገጥ ነው።(ዘፍ3:15) ዲያቢሎስ ስራው መዋሸት ነው።(ዮሐ8:44) ኢየሱስ ውሸትን የሚያፈርሰው በእውነት እውቀት ነው።(ዮሐ8:32) ኢየሱስ የመጣው ስለ አባታችን እውነት የሆነውን በመግለጥ ልጅ እንደሆንን እንዲገባን ነው።(1ዮሐ5:20) ልጅነታችንንም በቃልና በተግባር (በትምህርቱ እና በመስቀሉ ስራ) በርትቶ ገልጦታል ወደ ብርሀን አውጥቶታል።(ሉቃ24:19)
አንድ ጊዜ የልብ አይኖችህ ሲበሩ አንተና እግዚአብሔር ተለያይታችኃል ተብሎ የተነገረህ ሁሉ ውሸት መሆኑን ትረዳለህ። ከእግዚአብሔር ፍቅር ተለያይተህ የምትደበቅበት ምንም አይነት መንፈሳዊም መልካ ምድራዊም ቦታ እንደሌለ ታውቃለህ። ዛሬ ህይወትህን በተዋጀው ልጅነትና ነፃነት መኖር ጀምር። ችርስ😊
Comments
Post a Comment