እግዚአብሔር "በስሜ የተጠራው ህዝቤ" ሲል ምን እያለ ነው?
በመንፈሳዊ አለም ስርዓት ስም አንድን ግለሰብ ከሌላ ግለሰብ ለመለየት የሚሰጥ መጠሪያ ብቻ አይደለም። በእግዚአብሔር አለም ስም ማንነት ነው። ስም ማንነትህን የሚገልፅ አንድ ቃል ነው። ስም የማንነትህን ምንጭ የሚገልፅ ቃል ነው። ስም አቅምህን፣ አላማህንና ዘላለምህን የሚያብራራ ሀሳብ ነው። እግዚአብሔር ሰውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈጥር የራሱን የተሟላ "መልክና አምሳል" በማካፈል ፈጥሮታል። ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጥሯል ማለት ሰው እግዚአብሔር ሊጠራበት ወይም ሊታወቅበት ከሚችለው ከማንኛውም ስም (ማንነት) በታይ አይደለም ማለት ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር የሚጠራበት ስም ሁሉ አዳምም የሚጠራበት ስም ነው። ሀሌሉያ! ይሁን እንጂ አዳም በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ከተፈጠረው ከመንፈሱ ራሱን (ስሙን፣ ማንነቱን) ከመጥራት (ከማወቅና ከመመዘን) ይልቅ ከውጪ (በስጋ) ከሆነው፣ ካደረገውና ማድረግ ከሚፈልገው አንፃር መጥራት (መሰየም፣ መመዘን) ጀመረ። ይህ አዳም የወደቀበት ራስን (ስምን) በስጋ ከሰራው ስራ ተነስቶ የመጥራት (የመመዘን) የተሳሳተ አለማዊ ስርዓት ሰዎች ሁሉ ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ነው። በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጥሮ በእግዚአብሔር ስም (ማንነት) የተጠራው የሰው ዘር በማድረግና ባለማድረግ ስም (ማንነት) ላይ ወደቀ። ለአንድ ህፃን ወላጆች ከሚያወጡለት የምኞት መጠሪያ ስም በተጨማሪ ከአለም የህግ ስርዓት በታች የሚኖር ማነኛውም ሰው ከህፃንነት እያደገ ሲመጣ ከአስተዳደግ ሁኔታዎች፣ ከሚያልፉበት ታሪክ፣ ከአከባቢ፣ ከሀይማኖት፣ ከዘር፣ ካለውና ከሌለው ነገር፣ ካደረገውና ካላደረገው ነገር እንዲሁም ከሌሎች ውጫዊ ሁኔታዎች በመነሳት ስሙን (ራሱን፣ ማንነቱን) ለመሰየም ለመመዘን ለመጥራት ባሪያ ነው። እግዚአብሔር ግን ከአብረ...